ማህበሩ በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሠብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1113/2019 የተመዘገበና ገለልተኛና ለትርፍ ያልተቋቋመ ነው።
ማህበሩ ይፋዊ የምሠረታ ፕሮግራሙን በአዲስ አበባ ሲያካሂድ የፕላንና ልማት ሚኒሥቴር፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽንና የዳሸን ባንክ ተወካዮችን ጨምሮ ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
የተመሠረተው ማህበር በተለይም ያላደገውን የቢዝነስ ዘርፍ ጋዜጠኝነት በማጠናከርና የሚዲያ ባለሙያዎችን በመደገፍ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ በፕሮግራሙ ላይ ተነሥቷል።
የፕላንና ልማት ሚኒሥቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተርና አማካሪው አቶ ተሥፋዬ አባተ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያለውን ሀገራዊ እቅድ መነሻ በማድረግ ሥራዎችን በእውቀት ላይ በመመሥረት ለመሥራት ማህበሩ ትልቅ ሚና እንደሚጫዎት ገልጸው ማንኛውም የሚዲያ ባለሙያ መንግሥታዊ መረጃዎችን ከፕላንና ልማት ሚኒሥቴር ማግኘት እንደሚችልና በትብብር ለመሥራት ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል።
በሚኒሥቴሩ በኩል በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በሥነ ህዝብና በሌሎችም ሀገራዊ እቅዶችና ተግባራት ዙሪያ ክፍተቶችን በጥናት በመለየት ጠንካራ ሥራዎችን መሥራት በሚዲያው በኩል ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ፕሬዚደንት ዶክተር አምዲሳ ተሾመ በበኩላቸው የኢኮኖሚው ዘርፍ የሚዲያ ተቋማት የሁልጊዜ ሥራ መሆን እንደሚገባው ገልጸው ተቋማቸው ከማህበሩ ጋር በመሆን በኢኮኖሚው ተዋናዮችና በሚዲያ መካከል እንደ ድልድይ በማገልገል የላቀ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ነፃነት ተሥፋየ በበኩላቸው የቢዝነሥና ኢኮኖሚ ጋዜጠኝነት ዘርፍ እውቀት የሚጠይቅና የቢዝነሥ ተቋማትን ተግባራት በውል ከመለየት ጀምሮ በጥንቃቄ የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የቢዝነሥ ዜናዎች በአግባቡ ሢሠሩ ለሀገር ብልጽግና የሚኖራቸውን አበርክቶ ያክል የቁጥር ሥህተትም ሆነ የመረጃ ክፍተቶች ማህበረሠብን በመጉዳት ረገድ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የዳሸን ባንክ የብራንዲንግና ማርኬቲምግ ሲንየር ማናጀር አቶ ስለሺ ይልማ በበኩላቸው የሥረ ፈጠራን፣ ቴክኖሎጂና ወጣቶችን የሚደግፈው ባንካቸው አሁንም በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገልጸው የሚዲያ ባለሙያዎችም በዘርፉ ላይ ራሣቸውን ማብቃት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው የሚዲያ ማህበራትና በዘርፍ ሥፔሻላይዝ ሆነው የሚቋቋሙ ማህበራት መጠናከር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ማህበራት ከመቋቋማቸው ባለፈ ጠንካራ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸውና የሚዲያ ተቋማትም በባለሙያዎች የሚመሩና ሣይንሣዊ ሙያውን ያከበሩ መሆን እንዳለባቸው ጋዜጠኛ ጥበቡ አሥገንዝበዋል!
ማህበሩ በቀጣይም የጋዜጠኞችን አቅም ለመገንባትና የቢዝነሥና ኢኮኖሚ ዘርፍ ጋዜጠኝነት እንዲያድግ ሥትራቴጂ ነድፎ እየሠራ መሆኑ በይፋዊ ምሥረታ ማብሠሪያ ፕሮግራሙ ላይ ተጠቁሟል።15:28